የመጽሃፍ ቅዱስ ቦታዎች

በሶርያ ትገኝ የነበረችው ጥንታዊቷ አንጾኪያ ከክርስቶስ ልደት 300 አመታት በፊት የተመሰረትች ስትሆን በሮማ ግዛት ውስጥ ሦስተኛ ትልቅ ከተማ ነበረች። ከአንጾኪያ የሚበልጡ የነበሩት ሁለት ከተሞች የግብጽ እስክንድርያና የጣሊያን ሮም ብቻ ነበሩ ። አንጾኪያ በአሁኑ ጊዜ አንታኪያ ተብላ የምትታወቅ ሲሆን የምትገኘውም በቱርክ ነው። ብጂኦግራፊ አቀማመጧ ከሜድትራንያን ባሕር 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንዲሁም ከኢየሩሳሌም በስተ ሰሜን 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የምትገኘው።

መቄዶንያ በአዲስ ኪዳን ዘመን ከግሪክ በስተሰሜን የምትገኝ የሮማ ግዛት ነበረች። ሃዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሁለተኛው የሚሽን ጉዞው ላይ ሳለ ወደ መቄዶንያ ሄዶ እንዲያስተምር ራእይ አየ። ጳውሎስ በወንጌላዊነቱ የሚሽን ሥራ ላይ ካተኮረባቸው አራት ዋና ዋና አካባቢዎች አንዷ ይህቺው በግሪክ ሰሜናዊ ክፍል የምትገኘው መቄዶንያ ነበረች ። 

ከገሊላ ባሕር በስተ ሰሜን 40 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ከሄርሞን ተራራ ግርጌ የምትገኘው ፊልጶስ ቂሣርያ የዮርዳኖስ ወንዝን ከሚመግቡት ትልልቅ ምንጮች መካከል የአንዱ መፍለቂያ ስፍራ ናት። ይህ የተትረፈረፈ የውኃ አቅርቦት አካባቢው ለምና ለሃይማኖታዊ አምልኮ ማራኪ እንዲሆን አድርጎታል። በግሪካውያንና በሮማውያን ዘመን በዚህች ከተማ በርካታ የጣአኦታት ቤተ መቅደሶች ተገንብተው ነበር።