የሉቃስ ወንጌል የሚጀምረው ስለ ኢየሱስ መወለድ ብስራት በመናገር ነው: የመጥምቁ ዮሐንስ መወለድ፤ ኢየሱስ በግርግም ወደተወለደበት ወደ ቤተልሔም የማርያምና የዮሴፍ ጉዞ፤ እንዲሁም በማርያም በኩል የክርስቶስ የትውልድ ሐረግ። ኢየሱስ ባደባባይ ባስተማራቸው ትምህርቶች ውስጥ ፡ ሰለ ጠፋው አባካኙ ልጅ፣ ስለ ሀብታሙና ስለ አልዓዛር እንዲሁም ስለ ደጉ ሳምራዊ በሚነገሩ ታሪኮች አማካኝነት ፍጹም የሆነ ርኅራኄና ይቅርታ አሳይቷል። ብዙዎች ከሰው ልጆች አቅም በላይ በሆነው በዚህ እውነተኛ ፍቅር ቢያምኑም ሌሎች ግን በተለይም የሃይማኖት መሪዎች የኢየሱስን ትምህርት ሊቀበሉት ስላልቻሉ ይቃወሙት ነበር። የክርስቶስ ተከታዮች የደቀመዝሙርነትን ዋጋ እንዲያስተውሉ ይበረታታሉ። ጠላቶቹ ግን ሞቱን በመስቀል ላይ ይፈልጋሉ። በመጨረሻም ኢየሱስ በይሁዳ ተከድቶ ፍርድ ተበይኖበት ተሰቀለ። መቃብር ግን ሊይዘው አልቻለም! የእርሱ ትንሳኤ የጠፉትን የመፈለግ እና የማዳን አገልግሎቱን መቀጠል አስፈላጊነት ያረጋግጣል።