የኒቂያ የእምነት አንቀጽ

Nicean Creed of 325 AD

የኒቂያ ጉባኤ የተካሄደው ከክርስቶስ ልደት በኋላ በሮማ ንጉሠ ነገሥት ቄሣር በፍላቪየስ ቆስጠንጢኖስ ትእዛዝ በ 325 ዓመተ ምህረት ነበር። ኒቂያ የምትገኘው ከቁስጥንጥንያ በስተምሥራቅ በምትገኘው በትንሿ እስያ ነበር ። በኒቂያ ጉባኤ ላይ አፄ ቆስጠንጢኖስ የክርስቶስን አምላክነት በተመለከተ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ያለውን ግራ መጋባት፣ ውዝግብና አለመስማማት ለማስወገድ በሚል ዓላማ 318 የቤተ ክርስቲያን  ሊቃውንት ጳጳሳትንና ሌሎች መሪዎች የተገኙበትን ጉባኤ መርተዋል። የኒቂያ ጉባኤ የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት እና ዘላለማዊነት በከፍተኛ ሁኔታ አረጋግጦ በአብ እና በወልድ መካከል ያለውን መተካከል ተቀብሎ አጽንቶታል።   

 

 በ 318 ሊቃውንት በኒቂያ ጉባኤ የተደነገገ የእምነት አንቀጽ

                                 (325 ዓም)

ሁሉን በፈጠረ በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን ፡ ሰማይንና ምድርን የፈጠረ የሚታየውንና የማይታየውንም።

ዓለም ሳይፈጠር ከርሱ ጋር በነበረ የአብ አንድ ልጁ በሚሆን በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስም እናምናለን። ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ ፡ የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ በባህርዩ ከአብ ጋር የሚስተካከል።

ሁሉ በእርሱ የሆነ ፡ በሰማይም በምድርም ባለው ያለ እርሱ ምንም ምን የሆነ የለም።

ስለኛ ስለሰዎች እኛን ለማዳን ከሰማይ ወረደ በመንፈስ ቅዱስ ግብር ከቅድስት ድንግል ማርያም ፍጹም ሰው ሆነ።

ሰው ሆኖ በጴንጠናዊው ጲላጦስ ዘመን ስለኛ ተሰቀለ። መከራን ተቀበለ ፡ ሞተ ተቀበረም። በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሳ ፡ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተጻፈ በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ አረገ ፡ በአባቱ ቀኝ ተቀመጠ።

ዳግመኛ በምስጋና ይመለሳል። በሕያዋንና በሙታን ለመፍረድ ፡ ለመንግስቱም ፍጻሜ የለውም ፡:

በመንፈስ ቅዱስም እናምናለን። እርሱም ጌታ ሕይወትን የሚሰጥ ከአብ የሰረፀ ከአብና ከወልድ ጋራ በአንድነት እንሰግድለታለን ፡ እናመሰግነዋለን ፡ እርሱም በነብያት አድሮ የተናገረ ነው።

ከሁሉ በላይ ክብርት በምትሆን ሐዋርያት በሰሩዋት በአንዲት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን ፡ ኃጢአት በሚሰረይባት በአንዲት ጥምቀትም እናምናለን። የሙታንንም መነሳት ተስፋ እናደርጋለን ፡ የሚመጣውንም ሕይወት ለዘለዓለሙ ፡ አሜን።