ሐዋርያው ዩሐንስ

Apostle John Symbol (ሐዋርያው ዩሐንስ አርማ)

ሐዋርያው ​​ዮሐንስ በአራቱም ወንጌላት ውስጥ ከ12ቱ ሐዋርያት ቀደምት ከተባሉት ከሶስቱ መካከል አንዱ እንደነበረ ይታወቃል። እሱና ወንድሙ ያዕቆብ ሁለቱም የገሊላ ዓሣ አጥማጆች የነበሩ ሲሆኑ ፡ ኢየሱስ “የነጎድጓድ ልጆች” እያለ ይጠራቸው ነበር። ዮሐንስ ለኢየሱስ ክርስቶስ ከመቅረቡ የተነሳ ፡ ጌታችን ለፈጸማቸው ብዙ ተአምራት የአይን ምስክር ነበር። በተለይም ጌታችን በደብረ ታቦር ተራራ አምላክነቱን ያሳየበት ተአምራዊ ለውጥን ካዩት ከሶስቱ ሃዋርያት አንዱ ​​ዮሐንስ ነበር። በጌተሰማኒ በአትክልቱ ስፍራ ክርስቶስ የተሰቃየውን ስቃይ ጨምሮ፡ እስከ ስቅለተ ሞቱ ድረስ ዮሐንስ አብሮት ነበረ።

ሐዋርያው ዮሐንስ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ የዮሐንስ ወንጌል በመባል የሚታወቀውን 4ኛውን ወንጌል እንደጻፈ ይታወቃል። ከዚህም ሌላ ፡ ሶስት መልክቶችንና ፡ የዩሐንስ ራእይንም ጽፏል። የዮሐንስ ወንጌል በኢየሱስ እና በተወደደው ደቀ መዝሙር መካከል ስላለው ልዩ ፍቅር ብዙ ማጣቀሻዎችን ያካትታል። ዮሐንስ በመጨረሻው እራት ወቅት ራሱን በኢየሱስ ደረት አስጠግቶ ፡ “ጌታ ሆይ፥ ማን ነው የሚክድህ?።” ብሎ ጠይቋል። የዮሐንስ ወንጌል ከ12ቱ መካከል ዮሐንስ ብቻ በስቅለቱ በመጨረሻው ሰአት ከጌታው ጋር አብሮ እንደነበረ ይገልጻል:: ኢየሱስም በመስቀል ላይ ሆኖ ደቀ መዝሙሩንና እናቱን እርስ በርስ እንዲተሳሰቡ በአደራ ሰጥቷል። “አንቺ ሴት እነሆ ልጅሽ” ከዚያም ደቀ መዝሙሩን “እነሆ እናትህ” አለው ከዚያ ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት።

ከሌሎቹ ሶስት ወንጌሎች ይልቅ የዮሐንስ ወንጌል የኢየሱስን ሰብዓዊ ፍቅር አጉልቶ ያሳያል። በተለይ ለዮሐንስ ለራሱ፡ ለመግደላዊት ማርያም፣ ለቢታንያዋ ማርያምና ለእኅቷ ማርታ እንዲሁም ለወንድማቸው ለአልዓዛር ፍቅሩን እንዳሳየ ተጽፏል። አልዓዛርን ከሞት ከማስነሳቱ በፊት የሚያለቅሱትን እሆቶቹን አይቶ ክርስቶስ አብሮ እንዳለቀሰ የዮሐንስ ወንጌል ላይ ተጽፎ እናገኘዋለን። በእርግጥም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንደ ወዳጆች አድርጎ እንደተናገረ የሚገልጸው የዮሐንስ ወንጌል ብቻ ነው ።

“ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም:: እኔ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ብታደርጉ እናንተ ወዳጆቼ ናችሁ። ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፥ ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቄአችኋለሁና።”  የዮሐንስ ወንጌል - ምዕራፍ 15: 13-15

ዮሐንስ ለሚያስተምራቸው የክርስትና ማህበረሰብ የሚያስተምረው ዋነኛ የወንጌል መልዕክት “ኢየሱስ እንደወደደን እርስ በርስ የመዋደድ ሃላፊነት አለብን” የሚል ነበር። ይህም ዋና መልክት በጻፋቸው ሶስት መልክቶች ላይ ቁልጭ ብሎ ተቀምጧል። ዮሐንስ ስለ መጨረሻው እራት በሚገልጸው ዘገባ ላይ፡

“ኢየሱስ ከእራት በኋላ ልብሱንም አኖረ፥ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤ በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ፥ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ሊያጥብና በታጠቀበትም ማበሻ ጨርቅ ሊያብስ ጀመረ::”  የዮሐንስ ወንጌል - ምዕራፍ 13 ፡ 4-5

ኢየሱስ እንዲህ ዓይነቱን እውነተኛ ፍቅር እያሳየ የአምላክ ኃይል በፍቅር አገልግሎት እንደሚገለጽ ያስተምረናል።

በአፈ ታሪክ መሠረት ዮሐንስ እንደሌሎቹ ሐዋርያት የሞት ሰማዕትነት ባያጋጥመውም ወደ ፍጥሞ ደሴት በግዞት እንደቆየ ፡ በራእይም ጌታውን አይቶ እንደጻፈ እንማራለን። ከጊዜ በኋላም ወደ ኤፌሶን ሄዶ እስከ ዘመኑ መጨረሻ ድረስ የኤፌሶንን ቤተ ክርስቲያን ይመራ ነበር ።  አጋጣሚው ወይም ሁኔታው ምንም ይሁን ምን ሁሌ የሚሰብካት አጭር መልክት “ወንድሞችና እህቶች እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ።" የሚል ነበር። የጉባኤው አባላት አንዳንድ ጊዜ ለለውጥ ለምን ሌላ ስብከት አትሰብክለንም ብለው ሲጠይቁት ፡ “መጀመሪያ ፍቅር ይግባንና፡ ከዚያ በኋላ ወደ ሌላ ትምህርት እንሄዳለን።” እያለ ይመልሳላቸው ነበር።