01 የዮሐንስ ራእይ ጥናት መግቢያ

ወንድም አማረ ፈቃደ ታቦር

በጌታ ፈቃድና እገዛ የራእይ መጽሐፍ ጥናትን ዛሬ 1/16/23 ጀምሮ ማጥናት ጀምረናል (በሳምንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድናችኝ) ዛሬው መግቢያ እና ከምዕራፍ 22 በኋላ መዝጊያውን ጨምሮ፤ አንድ ምዕራፍ በአንድ ሳምንት በሚለው ቀመር ሲሰላ፣ መጽሐፉን ለመጨረስ ወደ ስድስት ወር ይፈጃል። ይህም አንድ ጥናት በአማካይ 18-19 ጥቅሶችን ያካትታል እንደ ማለት ነው።

// ከመግቢያው በጥቂቱ ፦

> (፩ኛ) ጸሐፊውን በተመለከተ፦

[ሐዋርያው] ዮሐንስ መሆኑ አራቴ (በመጀመሪያው ምዕራፍ ሦስት ጊዜ፤ ምዕራፍ 22 ውስጥ አንዴ) ስሙ ተጠቅሷል። በሐዋርያው ዮሐንስ ተጽፈዋል ተብለው የሚታወቁትን ሌሎች መጽሐፍት [የዮሐንስ ወንጌል፤ ፩ኛ፣ ፪ኛ እና ፫ኛ ዮሐንስ መልእክታት] የቋንቋ አጠቃቀም ጋር በማነጻጸር፤ የራእይ መጽሐፍን የጻፈው ዮሐንስ ኣይደለም የሚሉ አሉ። እንደ እኔ ዮሐንስ ራእይን ኣልጻፈም ከሚለው ሙግት ይልቅ፤ ሌሎቹን የጻፋቸው ዮሐንስ ኣይደለም የሚለው ይበልጥ ያስኬዳል እላለሁ (ልክ ናቸው ማለቴ ኣይደለም) ...

//

> (፪ኛ) መጽሐፉ መች ተጻፈ?

ብዙ የ20ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ምሁራን ከ90-እስከ-95 ዓ/ም ተጻፈ ይላሉ። የለም! ከኢየሩሳሌም ውድቀት በፊት (ወደ 65 ዓ/ም) ነው የተጻፈ ብለውም የሚሞግቱ አሉ። እነዚህን ሁለት አመለካከቶች ከሁለት የሮም ነገሥታት ጋር ያይዟቸዋል። ኒሮ እና ዲምሺያን ይባላሉ። ... /በግሌ ከመጀመሪያዎቹ ማለትም 90-95 ተጻፈ ከሚሉት ጋር እስማማለሁ ...

//

> (፫ኛ) የራእይ መጽሐፍ ትርጓሜን በተመለከተ፦

ዋናዎቹ አራት ናቸው፦

(3.1) "ኃላፊያውያን" [The Preterist View]፡ ብዙው የራእይ መጽሐፍ ክስተቶች ከ70 ዓ/ም ኢየሩሳሌም መውደቅና ከዚያ በፊት ባሉት ዓመታት ተፈጽመዋል ባይ ናቸው።

(3.2) "ታሪካውያን" (The Historical View): እያንዳንዱ ክስተት ለተወሰነ ወቅት (Dispensation) የሆነ (ወይም የሚሆን) ነው ባይ ናቸው።

(3.3) "ወደፊታውያን" (The Futurist View): እነዚህኛዎቹ ለሰባቱ የትንሿ እስያ አብያተ ክርስቲያናት ከተጻፈው መልእክት ውጭ (ምዕራፍ 2-3)፤ በተለይ ከምዕራፍ 6 እስከ 18 ወደፊት (ታላቁ መከራን ጨምሮ በታሪክ መጨረሻ) የሚሆኑ ናቸው ይላሉ። ምዕራፍ 19 የመጨረሻው ፍርድ ሆኖ፤ ምዕራፍ 20-22 ወደ ዘላለም መግባት ነው ባይ ናቸው።

(3.4) "አሳባውያን" (The Idealist View): እነዚህኛዎቹ (እኛም ነን ) ራእይ መጽሐፍ በመልካምና በክፉ፤ በእግዚአብሔር እና በሰይጣን ኃይላት፤ መኻል ያለውን ግጭት/ትግል በምልክት የሚያሳይ ነው ባይ ናቸው። /G.K. Bale የጻፉት መጽሐፍ የሚጥቀመው ትርጓሜ አሳባውያንን አመለካከት ተመርኩዞ ሆኖ፤ አንድ ደረጃ ከፍ የተደረገ ነው። "Eclecticism" ብለውታል፤ "a Redemptive-Historical Form of Modified Idealism" በማለት አስቀምጠውታል። /

//

> (፬ኛ) ልዩ ልዩ

- ምልክቶች፤

ቊጥሮች፤ ቀለማት፤ አውሬዎች፤ ... ወዘተ፡

በብዛት ያሉበት እጅግ ውብ መጽሐፍ ነው። ምሁራኑ ዮሐንስ ትርጉማቸውን ካስቀመጣቸው ምልክቶችን ውጭ ያሉትን ለመተርጎም የብሉይ ኪዳን መጽሐፍትን መጠቀም ያስፈልጋል ይላሉ። አያይዘውም፣ በተለይ የኢሳይያስ፣ ሕዝቅኤል፣ ዳንኤልና መዝሙር መጽሐፍት የመጽሐፉን ግማሽ ለመተርጎም ቀዳሚ መጽሐፍ ናቸው ብለው ይናገራሉ.....።

//

በራእይ መጽሐፍ ቊጥሮች የራሳቸው መልእክት ወይም ትርጉም አላቸው። በተለይ ሰባት ቊጥር (እስከ 50 ይደርሳል ይላሉ) - ፍጹምነትና ሙላትን [completeness] አመልካች ሆኖ ተቀምጧል።

ከ7 ሌላ፤ ሦስት (3) ፣ አራት (4) ፣ አሥር (10) ና አሥራ ሁለት (12) ቊጥሮችን በብዛት እናገኛለን።

በአጭር ቃላት ሲቀመጡ

- ሦስት (3): እግዚአብሔር-ሥላሴን የሚያመለክትበት ሁኔታ ያለውን ያህል፤ አስመሳዩን የክፋት (ሰይጣን) ኃይላትንም ያመለክታል፡ ዘንዶው፣ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይን ....

- አራት (4): ዓለምን፣ አቅጣጫን፣ ጠቅላላ የሰው ልጆችን ...

- አሥር (10) እና አሥራ ሁለት (12): እንደ ቊጥር 7 ሙላትና ፍጹምነትን አመልካች ናቸው።

ከእነዚህ ሌላ 1000 እጅግ በጣም ትልቅ ቊጥር ተደርጎ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን፤ ብዙዎች ከብዙ ነገርና ከብዙ ሰዎችና ሁኔታዎች ጋር የሚያይዙት የሰው ቊጥር ተብሎ የተቀመጠው 666ም አለ።

// ለሪፈረንስ ከታሰቡ ከታች ከተቀመጡት መጽሐፍት ውስጥ በቀዳሚነት በDr. G. K. BEALE በፈረንጅ ዓመት 1999 የታተመው "The Book of Revelation: a commentary on the Greek text" የሚለው ጥቅም ላይ ይውላል //

Reference
Century
Language