በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የእንድርያስ ጥሪ የማይረሳ ታሪክ ነው። እንድርያስና ዮሐንስ በመጀመሪያ የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ነበሩ ። መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስን የእግዚአብሔር በግ ነው ብሎ ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት (ዮሐ. 1፥35–37) ። ኢየሱስም እንድርያስን እና ዮሐንስን ሲከተሉት ተመልክቶ ቀኑን ከእርሱ ጋር እንዲያሳልፉ ጋበዛቸው (ዮሐ. 1፥38-39) ። እንድርያስ ቀኑን ከኢየሱስ ጋር ካሳለፈ በኋላ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን እርግጠኛ ሆነ። ከዚያም እንድርያስ መጀመሪያ ያደረገው ነገር ወንድሙን ስምዖንን አግኝቶ 'መሲሑን አገኘን' ብሎ መመስከር ነበር። ስምዖንንም ወደ ኢየሱስም አመጣው።" (ዮሐ. 1፥40–42) ። በዚህ መንገድ እንድርያስ ከኢየሱስ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ተከታዮች አንዱ ሲሆን ሌላ ሰውን ወደ ክርስቶስ ወይም ወደ ክርስትና ለማምጣት የመጀመሪያው ሰው ነው። የመጀመሪያው ወንጌላዊ ቢባል ስህተት አይሆንም።
ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲሄድ እንድርያስና ጴጥሮስ ዓሣ ለማጥመድ መረባቸውን ወደ ሐይቁ ሲጥሉ አገኛቸው። ኢየሱስም "ተከተሉኝ፣ እኔም ሰው አጥማጆች አደርጋችኋለሁ" አላቸው (ማቴ. 4፥19) ። መጽሐፍ ቅዱስ እንድርያስና ጴጥሮስ "ወዲያው” መረባቸውን ትተው ኢየሱስን እንደተከተሉ ይናገራል (ማቴ. 4፥20) ። እንድርያስና ጴጥሮስ በዮሐንስ 1 ላይ ከእሱ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት መሠረት በማድረግ ኢየሱስ ማን እንደሆነ ያውቁ ነበር፤ አሁን ደግሞ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ በይፋ ሲጠራቸው የእሽታ ምላሽ ሰጡ።
እንድርያስ የቤተሰቡን በዓሣ ማጥመድ ላይ የተመሰረተ የንግድ ስራውን ትቶ ክርስቶስን መከተሉ ፡ ለኛ ለክርስቲያኖች ሁሉ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል፤ ሁላችንም የተጠራነው "አስቀድመን መንግሥቱንና ጽድቁን እንድንፈልግ" ነው (ማቴዎስ 6 33) ፣ እናም የኢየሱስን ጥሪ ከመከተል ምንም ነገር እንዲከለከል መፍቀድ የለብንም። ኢየሱስ ለእንድርያስና ለጴጥሮስ 'ሰዎችን እንደሚያጠምዱ' ሲነግራቸው የሰዎችን ነፍስ ለማዳን እንደሚጠቀምባቸው ቃል ገብቷል። ደቀ መዛሙርቱም የማያወላውል የእሺታ ምላሽ ሰጡ ።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንድርያስ ጌታን ካገኘ በኋላ ሕይወቱ "ሰዎችን ማጥመድ" ላይ እንዳተኮረ እናያለን። እንድርያስ የራሱ ደቀ መዛሙርት እንደነበሩትም ተጽፏል። አንዳንድ ግሪኮች ኢየሱስን ለማየት በመፈለግ ከእንድርያስ ደቀ መዛሙርት አንዱ ወደሆነው ወደ ፊልጶስ ቀረቡ (ዮሐ. 12፥20–21) ። ፊልጶስ ግሪካውያን ምን እንደሚፈልጉ ለእንድርያስ ነገረውና እንድርያስና ፊልጶስ ጉዳዩን ለኢየሱስ አመጡለት (ዮሐ. 12፥22) ። እንድርያስ አህዛብ የሆኑትን ግሪኮችን ወደ ኢየሱስ ሲያመጣ የኢየሱስ ዓላማ ሰዎችን ሁሉ ለማዳን እንደሆነ እምነት ነበረው። እርሱም ትክክል ነበር። ኢየሱስም "የሰው ልጅ የሚከበርበት ሰዓት ደርሶአል" በማለት መስቀሉን በመጥቀስ መልስ ሰጠ (ዮሐ. 12፥23)። የእሱ ሞትና ትንሣኤ ከሁሉም ዘሮች ፣ ከኃይማኖቶችና ከቤተሰብ የተውጣጡ ሰዎች በሙሉ የሚድኑበት መንገድ ነው ። እንድርያስ ደግሞ ከአይሁድ ሕዝብ ባሻገር በወንጌላዊነት ሥራ ከተካፈሉት ሰዎች መካከል አንዱ ነው።
ከበዓለ ጴንጤቆስጤ በኋላ እንድርያስ ምን እንዳከናወነ መጽሐፍ ቅዱስ አይዘግብም ። ዩሲቢየስ የተባለው የጥንት የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ እንድርያስ ከጥቁር ባሕር በስተ ሰሜን ድረስ ሄዶ ወንጌልን እንዳስተማረ ተናግሯል ። ለዚህም ነው እንድርያስ የሩሲያ ቅዱስ ጠባቂ ነው የሚባለው። በተጨማሪም የስኮትላንድም ጠባቂ ነው ይባላል።
በመጨረሻም እንድርያስ በአቴንስ አቅራቢያ በምትገኘው በደቡባዊ ግሪክ በአካይያ በስቅላት ተሰዋ። እንደ አንድ አፈ ታሪካዊ ዘገባ የአንድ የሮም አገረ ገዢ ሚስት የእንድርያስን ትምህርት ሰምታ ጌታን ተቀበለች። ይህም ባሏን አስቆጥቶት ሚስቱ ለኢየሱስ ክርስቶስ የጀመረችውን አምልኮ እንድታቆም ጠይቋት እሷም ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ባለመሆኗ አገረ ገዢው ተናዶ እንድርያስን በስቅላት እንዲቀጣ ፈረደበት። እንድርያስም እንደ ጌታው መሰቀሉን ጽድቅ አርጎ ቆጥሮ በደስታ ተሰዋ።