ወንድም ዕዝራ እና ወንድም አረጋይ
ወደ ኤፌሶን ሰዎች ምዕራፍ 4
1 እንግዲህ በጌታ እስር የሆንሁ እኔ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤
2 በትሕትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤
3 በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ።
4 በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤
5 አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤
6 ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ።
7 ነገር ግን እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን።
8 ስለዚህ። ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ ይላል።
9 ወደ ምድር ታችኛ ክፍል ደግሞ ወረደ ማለት ካልሆነ፥ ይህ ወጣ ማለትስ ምን ማለት ነው?
10 ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው።
11 እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ፤
12-13 ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ።
14 እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕፃናት መሆን ወደ ፊት አይገባንም፥
15 ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ፤
16 ከእርሱም የተነሣ አካል ሁሉ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሠራ፥ በተሰጠለት በጅማት ሁሉ እየተጋጠመና እየተያያዘ፥ ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል።
Language