ሐዋርያው ቶማስ

Apostle Thomas Symbol (የሃዋርያው ቶማስ አርማ)

ሐዋርያው ቶማስ ከአሥራ ሁለቱ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት አንዱ ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ደግሞ ዲዲሞስ (ዮሐንስ 11 16፤ 20 24) እየተባለ ይጠራ ነበር። ዲዲሞስ ግሪክኛ ሲሆን ቶማስ ደግሞ የዕብራይስጥ ስም ነው። ሁለቱም ትርጉሞች "መንታ" ማለት ነው። በማቴዎስ፣ በማርቆስና በሉቃስ ወንጌሎች ውስጥ ቶማስ በሐዋርያት ዝርዝር ውስጥ ብቻ ነው የተጠቀሰው (ማቴዎስ 10 3፤ ማርቆስ 3 18፤ ሉቃ 6 15)። በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ቶማስ በሁለት ዋና ዋና አጋጣሚዎች ውስጥ ግንባር ቀደም ሚና ተጫውቷል።

ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ሊያበቃ በተቃረበበት ወቅት በይሁዳ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ጌታን ለመግደል ሴራ ጠንስሰው ነበር። ወዳጃቸው አልዓዛር ሊሞት እንደሆነ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ዜና የደረሳቸው በዚህ ወቅት ነበር (ዮሐ. 11፥1–3)። ደቀ መዛሙርቱ ሕይወታቸውን እንዳያጡ በመፍራት ኢየሱስ፣ በኢየሩሳሌም አቅራቢያ ወደምትገኘው የአልዓዛር የትውልድ ከተማ ወደ ቢታንያ እንዳይመለስ ለማሳመን ሞክረው ነበር። ኢየሱስ ግን ለመሄድ ቆርጦ ነበር። ቶማስም አብረውት ለነበሩት ደቀ መዛሙርት "እኛ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንሞት ዘንድ እንሂድ" ብሎ ተናገረ (ዮሐ. 11፥16)። ቶማስ ከኢየሱስ ጋር መከራን እስከ ሞት ደረስ ለመቀበል ዝግጁ መሆኑ ምን ያህል ታማኝ እንደሆነ ያሳያል ።

ከቶማስ ህይወት ለጌታው ምን ያህል ከፍተኛ ታማኝነት እንደነበረው እንማራለን፣ ነገር ግን ቶማስ ተጠራጣሪ ባህርይ ነበረው። በትንሣኤው ቀን፣ ጌታ ኢየሱስ ለተወሰኑ ደቀ መዛሙርቱ በተዘጋ ክፍል ውስጥ በታየበት ሰአት ቶማስ ከእነርሱ ጋር አልነበረም (ዮሐ. 20፥19–24)። ከዚያ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ከሞት የተነሳውን ጌታ እንዳዩ ለቶማስ ሲነግሩት እንዲህ ሲል መለሰ፥ “የችንካሩን ምልክት በእጆቹ ካላየሁ : ጣቴንም በችንካሩ ምልክት ካላገባሁ : እጄንም በጎኑ ካላገባሁ አላምንም አላቸው" (ዮሐ. 20፥25)።

በዚህም ንግግሩ ቶማስ በታሪክ ለዘመናት ሁሉ የሚታወስበትን ቅጽል ስም አገኘ - ተጠራጣሪው ቶማስ። ለቶማስና ለብዙዎቻችንም ጭምር ማየት ማመን ነው። ይሁን እንጂ ቶማስ የነበረው ጥርጣሬ እውነትን እንደሚክድ ዓለማዊ ተቃውሞ አይደለም ። ጥርጣሬው እውነትን ለማወቅ የሚያደረገውን እውነተኛ ጥረትን ያመለክታል።

ቀደም ሲል፣ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ስለ መሄዱ እና ወደ አባቱ ቤት ሄዶ ለእነርሱ ቦታ ለማዘጋጀት እንደሚሄድ ነግሮአቸው ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ እሄዳለሁ የሚለው ወዴት እንደሆነ ግራ ገብቷቸው ነበር። ቶማስ ሐቀኛ ጥርጣሬውና እውነትን መፈለጉ አነሳስቶት  "ጌታ ሆይ፣ ወዴት እንደምትሄድ አናውቅም፤ ታዲያ መንገዱን እንዴት ማወቅ እንችላለን?" ብሎ ጠይቋል።(ዮሐንስ 14 5)። ኢየሱስም መልሶ ለቶማስ "እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም እኔ ነኝ ። በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም" (ዮሐ. 14 6)። ኢየሱስ እየተናገረ ያለው ስለ መንገድ ወይም ስለ ቦታ ማወቅ ሳይሆን የህይወት በር የሆነውን ጌታን ስለማወቅ ነው።

ቶማስ ኢየሱስ መነሳቱን ለማመን የሚያስችል ማስረጃ እንደሚያስፈልገው ለሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ሲነግራቸው በሐቀኝነት መናገሩ ነበር ። ከልብ የመነጨ እምነት በቅን ልቦና መመርመርን አይከለክልም ። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ ከስምንት ቀናት በኋላ ደቀ መዛሙርቱ እንደገና ተገናኙ። በዚህ ጊዜ ቶማስ በቦታው ነበር ።  ኢየሱስ እንደገና ተገለጠላቸውና ቁስሉን እንዲነካና ራሱን እንዲያይ ኢየሱስ ቶማስን ጋበዘው። "ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን አለው።" (ዮሐ. 20፥27)። ኢየሱስ ቶማስ ምን ማመን እንዳለበት ያውቅ ስለነበር ማስረጃውን አሳየው። ቶማስም። “ጌታዬ አምላኬም” ብሎ መለሰለት። (ዮሐ. 20፥28)

ኢየሱስ በፍቅር የቶማስን ጥርጣሬ ቀርፎ ወደ እምነት እንዲመለስ መርቶታል። ስለ ጥርጣሬያችንና ስለ ጥያቄዎቻችን ለእግዚአብሔር ሐቀኞች መሆን እንችላለን፤ አምላክ ነውና በውስጣችን ያለውን ጥርጣሬ ይረዳል ፡ እምነታችንንም ያጠነክርልናል። እንደ ቶማስ ሁሉ እኛም ኢየሱስ ማን እንደሆነ ሙሉ በሙሉ ተረድተን "ጌታዬና አምላኬ!" ብለን እንናዘላለን (ዮሐ. 20፥28)።

ኢየሱስ የቶማስን እምነት ካጸናለት በኋላ ወደፊት ለሚከተሉት ክርስትያን አማኞች በጣም ጠቃሚ የሆነ የእምነት መልክት እንዲህ በማለት ተናግሯል - "ቶማስ ሆይ ፣ እኔን ስለ አየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው አለው" (ዮሐ. 20፥29) እነዚህ ቃላት ከሞት የተነሳውን ክርስቶስን ሳናየው በእርሱ ያመንነውን ሁላችንንም ለማበረታታት እና ለማጽናት ይጠቅማሉ።

ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ኢየሱስ በገሊላ ባሕር ሲገለጥላቸው ቶማስ ጴጥሮስና ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ዓሣ ሲያጠምዱ ነበር (ዮሐ. 21፥2)። ቶማስ ለመጨረሻ ጊዜ በመጽሃፍ ቅዱስ  የተጠቀሰው በሐዋርያት ሥራ ላይ ሲሆን ከደቀ መዛሙርቱ መካከል እንደአንዱ ተዘርዝሮ ይገኛል።

በአፈ ታሪክና ከመጽሃፍ ቅዱስ ውጪ በተጻፉ ጽሑፎች እንደምንረዳው ሃዋርያው ቶማስ ወንጌልን ወደ ደቡብ ሕንድ እንደወሰደና ለእምነቱ ሲል ሰማዕት እንደሆነ ይነገራል። የዚህ አፈ ታሪክ እውነታ ምንም ይሁን ምን በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ፖርቹጋላውያን የመርከብ ተጓዦች በደቡባዊ ሕንድ ማላባር የባሕር ዳርቻ ላይ ባረፉ ጊዜ በሐውርያው ቶማስ ወንጌላዊነት የተመሰረተ ቤተ ክርስቲያንና የክርስቲያን ማኅበረሰብ አግኝተዋል ።  እስከዛሬ ድረስ የዚህ ማኅበረ ራሳቸውን የሃዋርያው ቅዱስ ቶማስ ክርስቲያኖች ብለው ይጠራሉ።

ባጠቃላይ "ተጠራጣሪ ቶማስ" የሚለው ቅጽል ስም ተገቢ አይመስልም። እርግጥ ነው፣ ቶማስ እውነትን ከመቀበሉ በፊት የክርስቶስ ትንሣኤ ተአምር መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ ጠይቆ ነበር። ለሌሎቹ ሃዋርያት ጥርጣሬ የተሞላበት መልስ ቢሰጥም ፡ ይሄ መልሱ ብቻ እሱን መለያ መሆን አይገባውም። ሐዋርያው ቶማስ በታማኝነቱ፣ ለወንጌል ታዛዥነቱ፣ እና በእምነቱ ይበልጥ ሊታወቅ ይገባል።

Video