ወንድም አማረ ፈቃደ ታቦር
21 የዮሐንስ ራእይ ምዕራፍ 16:12-21
12 ስድስተኛውም ጽዋውን በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ ላይ አፈሰሰ፤ ከፀሐይም መውጫ ለሚመጡ ነገሥታት መንገድ እንዲሰናዳላቸው ውኃው ደረቀ።
13 ከዘንዶውም አፍና ከአውሬው አፍ ከሐሰተኛውም ነቢይ አፍ ጓጕንቸሮች የሚመስሉ ሦስት ርኵሳን መናፍስት ሲወጡ አየሁ፤
14 ምልክት እያደረጉ የአጋንንት መናፍስት ናቸውና፥ በታላቁም ሁሉን በሚገዛ በእግዚአብሔር ቀን ወደ ሚሆነው ጦር እንዲያስከትቱአቸው ወደ ዓለም ሁሉ ነገሥታት ይወጣሉ።
15 እነሆ፥ እንደ ሌባ ሆኜ እመጣለሁ፤ ራቁቱን እንዳይሄድ እፍረቱንም እንዳያዩ ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ ብፁዕ ነው።
16 በዕብራይስጥም አርማጌዶን ወደሚባል ስፍራ እስከተቱአቸው።
17 ሰባተኛውም ጽዋውን በአየር ውስጥ አፈሰሰ፤ ከመቅደሱም ውስጥ። ተፈጽሞአል የሚል ታላቅ ድምጽ ከዙፋኑ ወጣ።
18 መብረቅና ድምጽም ነጎድጓድም ሆኑ፥ ትልቅም የምድር መናወጥ ሆነ፤ ሰው በምድር ከተፈጠረ ጀምሮ እንዲህ ያለ ታላቅ መናውጥ ከቶ አልነበረም፤ ከሁሉ በለጠ።
19 ታላቂቱም ከተማ በሦስት ተከፋፈለች፥ የአሕዛብም ከተማዎች ወደቁ። ታላቂቱም ባቢሎን የብርቱ ቍጣው ወይን ጠጅ የሞላበትን ጽዋ እንዲሰጣት በእግዚአብሔር ፊት ታሰበች።
20 ደሴቶችም ሁሉ ሸሹ ተራራዎችም አልተገኙም።
21 በሚዛንም አንድ ታላንት*ፍ1* የሚያህል ታላቅ በረዶ በሰዎች ላይ ከሰማይ ወረደባቸው፤ ሰዎቹም ከበረዶው መቅሰፍት የተነሳ እግዚአብሔርን ተሳደቡ፥ መቅሰፍቱ እጅግ ታላቅ ነውና።
ፍ1 አንድ ታላንት ሦስት ፈረሱላ የሚያህል ነው።
Language